የተለያዩ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ ምርታማነታቸው ከፍ ያሉና በሽታን መከላከል የሚችሉ የተለያዩ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአሰላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል።
ኮርፖሬሽኑ በ2017/18 የምርት ዘመን በአጠቃላይ በ20ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተባዙ የ22 ሰብሎች 90 ዝርያዎች ምርት እየሰበሰበ ሲሆን፣ ለማባዛት ያቀደው 460ሺህ ኩንታል ዘር መሆኑም ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአሰላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተወካይ ማንያዘዋል ለማ እንዳሉትም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ አርሶ አደሩ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ በሚያደርገው የእርሻ እንቅስቃሴ ውስጥ ግብዓቶችን በማቅረብ ነው።
ጽሕፈት ቤቱ የስንዴ፣ የጤፍ እና የሌሎችም ሰብሎች ምርጥ ዝርያዎችን እያባዛ በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በ2017/18 በቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት የተባሉ ምርጥ ዘሮችን በ1ሺህ 964 ሄክታር መሬት ላይ እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም 49ሺህ 205 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሚባዛው ምርጥ ዘር ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአየር ንብረት ጋር የሚስማማ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚያሰራጫቸው ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ ምርት በማስገኘት የምርት መጠንና ጥራት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የዘር ጥራት፣ ቁጥጥርና ክትትል ቡድን መሪ አዳነ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ ጥራት ያላቸው ዘሮች እና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ በመሆናቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን መወጣት ያስችላሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአሰላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለበጋ መስኖ እርሻ የሚውል ከአሥራ አንድ ሺህ አምስት መቶ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ መሆኑንም አስታውቋል።