በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራት ተከናውነዋል
አዳማ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በሩብ ዓመቱ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የማጎልበት ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የማጎልበት ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይም የሴቶችን መንግስታዊ የስራ ኃላፊነት በማሳደግ ለሀገር ልማት የሚተጉበትን እድል ለማስፋት መሰራቱን አክለዋል።
የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጉላት ያለሙ ስልጠናዎችን በመስጠት በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከወዲሁ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በሩብ ዓመቱ ሦስት ሺህ ሴቶች በከተማና ገጠር ግብርና እንዲሰማሩ በማድረግ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ ባለፈም በቦረና ዞን ያቤሎ ከተማና በምእራብ ሸዋ ኤጀሬ ወረዳ አነስተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን በእንስሳት ማድለብና በወተት ላሞች እርባታ ስራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሴቶች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
የሴቶችን መብትና ደህንነት ለማረጋገጥም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰራቱን አንስተዋል።
የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የጥቃት አድራሾችን ጥቆማ ለመቀበል 919 ነጻ የስልክ መስመር መዘርጋቱን አንስተዋል።
በጥቃት አድራሾች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከፖሊስና ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የሴቶችን ጥቃት የማይቀበል ማህበረሰብን ለማፍራትና የ''ነጭ ሪቫን'' ቀንን በማስመልከት የአንድ ወር ንቅናቄ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
ይህም ለጥቃት የተጋለጡ ወገኖች የስነ ልቦናና የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አክለዋል።