ቀጥታ፡

የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የጉብኝት ስርዓትን ለማዘመን እየተሰራ ነው

ጎንደር ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በጎንደር የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የጉብኝት ስርዓትን የማዘመን ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአብያተ መንግስቱን የጉብኝት ስርዓት ለማዘመን የመግቢያ ቲኬት የዲጂታል አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀመርም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፡ የጎንደር  አብያተ መንግስትን የጉብኝት ስርዓት ለማዘመን አዳዲስ የጉብኝት ፓኬጆችን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡


 

በዚህም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ሲስተናገዱበት የቆየውን የወረቀት የመግቢያ ቲኬት በማስቀረት ቀልጣፋና ዘመናዊ የዲጂታል ትኬት አገልግሎት በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል፡፡

የዲጂታል ትኬት አገልግሎቱን ለማስጀመርም ቢሮው ከክልሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመሆን ሶፍትዌር የማልማት ስራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የዲጂታል ትኬት አገልግሎቱን በመጪው የጥምቀት በዓል ለማስጀመር መታቀዱን የጠቆሙት አቶ መልካሙ ቱሪስቶች በፈለጉበት ሰዓትና ጊዜ አስቀድመው በኦን ላይን ቲኬት መቁረጥ እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል፡፡ 


 

ለአብያተ መንግስቱ በተደረገው እድሳትም የመብራት ቴክኖሎጂና የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙ በመሆኑ ከቀን በተጨማሪ ምሽት ላይ ለማስጎብኘት አዲስ የጉብኝት ፓኬጅ ማዘጋጀት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ከአዳዲስ የጉብኝት ፓኬጆች መካከልም በቢሮውና በቱሪዝም ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በቅርቡ በይፋ የተጀመረው "ህይወት በአብያተ መንግስት ትዕይንት" ፕሮጀክት ቀጣይ እንዲሆንም ይደረጋል ብለዋል።


 

የነገስታቱን የቀደመ ታሪክና ክዋኔ ወደ ኋላ በምልሰት በማስታወስ የሚቀርበው የኪነ ጥበብ ዝግጅት የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።   

መንግስት ለቱሪዝም ልማቱ በሰጠው ልዩ ትኩረት የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ሙሉ እድሳት ከተደረገለት በኋላ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለጉብኝት ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም