ቀጥታ፡

በሽሬ እንዳስላሴና አካባቢው የኃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናወነ

ሽሬ እንዳስላሴ ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ሽሬ እንዳስላሴና አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የትራንስፎርመሮች ተከላ እና የኃይል ተሸካሚ መስመሮች ዝርጋታ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽሬ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኪዳኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሽሬ እና አካባቢው የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በሪጅኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት ከ984 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ መከናወናቸውን ተናግረዋል። 

በሪጅኑ በሚገኙ ሽሬ እንዳስላሴ፣ በአክሱም፣ በአድዋ እና በሌሎች ስምንት ከተሞች የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የትራንስፎርመር ተከላና ያረጁ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመተካት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። 

በዚህም የ108 ኪሎ ሜትር መካከለኛና ዝቅተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ዝርጋታ፣ የ119 ትራንስፎርመሮች ተከላና የ55 ኪሎ ሜትር የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት የመተካት ሰራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል። 


 

እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለማዘመንም ጊዜ ቆጣቢ የተለያዩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ መፈፀሚያ አማራጮች በሪጅኑ ስር በሚገኙ 15 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት መዘርጋቱንም ተናግረዋል። 

ሪጅኑ በተያዘው የበጀት ዓመት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካትና አገልግሎቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። 


 

ከሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በላይ ኃይሉ እና አቶ ጌታቸው ካህሳይ፤ አገልግሎቱ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋትና ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራርን ለመዘርጋት የጀመረው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

የቆዩ ምሰሶዎችን የተሻለ ደረጃ ባላቸው የመቀየር እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በአዲስ መልክ መቀየራቸው የኃይል መቆራረጥን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም