ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የጎብኝዎች ቁጥር ከፍተኛ እድገት እያሳየ ነው

ሰመራ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የአፋር ክልል የሰው ልጅ ቅሪተ አካል መገኛነቱ ከመታወቁ ባሻገር የኤርታሌ እሳተ ገሞራ፣ የዳሎል ዝቅተኛ ስፍራ መገኛ መሆኑና ሌሎችም በክልሉ የሚገኙ ድንቅ የተፈጥሮ መስህቦች ለቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ አድርጎታል።


 

ክልሉ በቱሪዝም መስህብነት በቢጫ ቀለም የተንቆጠቆጠው የዳሎል አካባቢ፤ ዓመቱን ሙሉ ባለማቋረጥ የሚንቀለቀለው አስደናቂው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ፣ የጨው ምርት የሚታፈስበት አፍዴራ ሐይቅ እና የሌሎችም አስደናቂ ስፍራዎች መገኛ ነው።

በመሆኑም እነዚህና ሌሎችም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች አይነተኛ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻና የፓርኮች ልማት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሐሰን ተናግረዋል።


 

በዚህም በዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ 1 ሺህ 300 የውጭ አገራት ቱሪስቶች በአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው ከዚህም ከ 88 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።


 

የክልሉን የቱሪዝም ሃብት በስፋት የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ እና የሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ ማረፊያን ጨምሮ ሌሎችም ተጨማሪ የመስህብ ስፍራዎችን ምቹ ማድረግ በመቻሉ ለዘርፉ እድገት አንዱ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

ዓመቱን ሙሉ ባለማቋረጥ የሚንቀለቀለው አስደናቂው የኤርታሌ እሳተ ገሞራ፣ ዳሎል እና አሎለበድ ፍልውሃ በአካባቢው የብዙዎችን ቀልብ እየሳቡ ያሉ የመስህብ ስፍራዎች ሆነዋልም ብለዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መኖሩም ለጎብኝዎች ፍሰት መጨመር ምክንያት ስለመሆኑም አቶ መሐመድ ገልጸዋል።


 

በቢሮው የቱሪዝም ግብይትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አብዱ አህመድ፤ በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል።

ከዚህም ውስጥ የቱሪዝም ማህበራት የአገልግሎት ክፍያ በአግባቡ እንዲከናወን መደረጉ አንዱ ሲሆን አስጎብኝዎች ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት የአሰራር መመሪያ መሻሻሉም ውጤት እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም