ለቡና ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት በወጪ ንግድ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለቡና ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት በወጪ ንግድ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ለቡና ምርትና ምርታማነት የሰጠው ትኩረት እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በዘርፉ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን እውቅና የተሰጣቸው የቡና ላኪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለ2017 እቅድ አፈጻጸም መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የእውቅና መርኃ ግብር አከናውኗል።
እውቅና ከተሰጣቸው ቡና ላኪዎች መካከል የኤስ ኤ ባግሬሽ ቡና ላኪ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አብደላ ባግሬሽ ባለፉት ዓመታት በቡና ንግድ ላይ ከፍትኛ ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ በቡናው ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት መታየቱን ገልጸው፤ በተለይም በዚህ ዓመት በነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ለውጭ ገበያ ያቀረቡት ቡና በመጠን እና ገቢ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ቡና በጥራት ለዓለም ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
መንግስት በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የወሰዳቸው እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን ጠቁመዋል።
የብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች የዘርፉን አፈጻጸም በጉልህ እንዳሳደጉት ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን እያደረገ ያለው የክትትል እና ድጋፍ ስራ ለዘርፉ አፈጻጸም ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእርሻ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ፈለቀ ታደሰ በበኩላቸው፤ እውቅናው በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
መንግስት የቡናን ምርታማነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለአብነትም ያረጁ የቡና ተክሎችን በማደስ እንዲሁም አዳዲስ በመትከል የተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ብዙዎች ወደ ኤክስፖርት እንዲያዘነብሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የእሴት ቡና መስራች እና ስራ አስኪያጅ እሴት ባረጋ ተቋማቸው እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
መንግስት ያደረጋቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ማበረታቻዎች ለስራቸው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመጥቀስ፤ በቀጣይም እንደ ሀገር በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
መንግስት ቡና ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለሚያቀርቡ አካላት በሰጠው ማበረታቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጫካ ቡና መስራች እና ባለቤት ብስራት በላይ ናቸው።
በተፈጠረላቸው መልካም እድል በመጠቀም ለላቀ ስኬት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡