ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደጋቶ ኩምቤ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመርና የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል ያለመ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደጋቶ ኩምቤ፤ ማሻሻያው ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የተለያዩ ተቋማት ክፍት እንዲደረጉ አስችሏል ብለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ ወደ ገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲሸጋገር ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ይህም ሀገራዊ ምጣኔ ሃብትን አሻሽሏል፤ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢን ምቹ አድርጓል እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ አነቃቅቷል ነው ያሉት፡፡
በ2017 በጀት አመት ብቻ 525 ለሚሆኑ የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስታውሰው፤ በካፒታል ደረጃ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ለውጭ ባለኃብቶች ክፍት መደረጋቸው ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከከቱን ገልጸዋል፡፡
ለኢንቨስትመንት ምቹ ያልነበሩ የህግ እና የአሰራር ክፍተቶች ተለይተው እንዲሻሻሉ መደረጋቸውን አንስተው፤ ይህም የኢንቨስተሮች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ጨምረው አመላክተዋል፡፡
በ2018 በጀት አመት የመጀመሪያወቹ አራት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ የ4ሺህ ኢንቨስተሮችን ፕሮፋይል የማጣራት ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡