በጤና መድህን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እያገኘን ነው-ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጤና መድህን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እያገኘን ነው-ተጠቃሚዎች
ሮቤ ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና መድህን አገልግሎት ጤናችንን ለመጠበቅና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንድናገኝ አግዞናል ሲሉ በባሌ ዞን የዲንሾ ወረዳ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ ።
በወረዳው የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ አባላት መካከል ወይዘሮ ሙኒራ ኡስማን እንዳሉት አንድ ጊዜ በከፈሉት አነስተኛ ገንዘብ የህክምና አገልግሎትን በማግኘት የቤተሰባቸውን ጤና መጠበቅ ችለዋል።
የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች በመርሃ ግብሩ እንዲታቀፉ በፈጠሩላቸው ግንዛቤ በአባልነት ተመዝግበው ያለ ስጋት የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አስቀድመው በከፈሉት የአባልነት መዋጮ ዓመቱን ሙሉ ሳይጉላሉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በመርሐ ግብሩ የታቀፉት የወረዳው ነዋሪ አቶ ሱሌይማን አብዱረህማን ናቸው።
በማሳያነትም ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ለማሳካም የተጠየቁትን ከፍተኛ ወጪ አገልግሎቱ በመሸፈኑ ከስጋትና እንግልት እንደታደጋቸው ገልጸዋል።
የዲንሾ ወረዳ ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ወርቁ እንደገለፁት፤ የህብረተሰብ ተሳትፎና ግንዛቤን በማሳደግ ከወረዳው 10 ሺህ አባወራዎች መካከል ከ9 ሺህ በላይ የሚሆኑትን የማህበረሰብ የጤና መድህን አባል ማድረግ ተችሏል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባላትን የመረጃ አያያዝን ዲጂታላይዝ በማድረግም ተጠቃሚዎቹ ሳይጉላሉ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድተዋል።
ይህም ወረዳው በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴል ሆኖ እንዲመረጥ ማድረጉን አክለዋል።
የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘገየ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በዞኑ 10 ወረዳዎች ውስጥ በ2017 የበጀት ዓመት ከ763 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ዞኑ ከጤና መድህን አገልግሎት አባላቱ የሚሰበስበውን ገንዘብ በአንድ ቋት በማድረግ ተገልጋዩ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ከ30 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች በጤና መድህን ስርዓት መታቀፋቸውን ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።