ቀጥታ፡

የዓለም ዓይኖች ያረፉበት የአርሰናል እና ባየር ሙኒክ ተጠባቂ ፍልሚያ 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 5 ሰዓት ላይ አርሰናል እና ባየር ሙኒክን በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያገናኘው ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ትኩረት ስቧል።

በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊጉ መርሃ ግብር ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ያሸነፉት እነዚህ ሁለት ክለቦች ናቸው።

ባየር ሙኒክ እና አርሰናል ተመሳሳይ 12 ነጥብ እና 11 የግብ ክፍያ አላቸው። ሙኒክ ብዙ ጎል ባገባ የአንደኝነት ደረጃን ይዟል። አርሰናል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ምንም ግብ ያልተቆጠረበት ብቸኛው ቡድን ነው። 

ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ15ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 14 ጨዋታዎች አርሰናል ስምንት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ባየር ሙኒክ ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።


 

አርሰናል በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ 30 ግቦችን ሲያስቆጥር ባየር ሙኒክ 15 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ቡድኖቹ በውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2023/24 ሩብ ፍጻሜ ላይ ነበር። ባየር ሙኒክ አርሰናልን በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል።

ባየር ሙኒክ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ስድስት ጊዜ አንስቷል። አርሰናል ውድድሩን አሸንፎ አያውቅም። 

በዘንድሮው የውድድር ዓመት አርሰናል እና ባየር ሙኒክ በአውሮፓ ላይ ድንቅ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛል።

አርሰናል ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 15 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። መድፈኞቹ በ29 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመሩ ነው። 

ባየር ሙኒክ ዘንድሮው በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። 16 ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በ31 ነጥብ ቡንድስሊጋውን እየመራ ይገኛል። 


 

ሁለቱ ቡድኖች ለእግር ኳስ ቤተሰቡ አዝናኝ እና ጠንካራ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የ44 ዓመቱ ጣልያናዊ ማርኮ ጉይዳ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በሌሎች መርሃ ግብሮች የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ፣ ኦሎምፒያኮስ ከሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑል ከፒኤስቪ አይድሆቨን፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ከኢንተር ሚላን፣ ኢንትራክት ፍራንክፈርት ከአትላንታ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ከክለብ ብሩዥ በተመሳሳይ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኮፐንሃገን ከካይራት አልማቲ እና ፓፎስ ከሞናኮ በተመሳሳይ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ45 ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም