የመቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የመቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 9 ሰዓት መቻል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ይጫወታሉ።
መቻል በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
መቻል በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ እስከ አሁን ያከናወናቸውን አምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። 20 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በሌላኛው መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ካካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው። አምስት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦች ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በዘጠኝ ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው ባህር ዳር ከተማ በሰባተኛው ሳምንት በይርጋጨፌ ቡና ካጋጠመው ሽንፈት ለማገገም፣ በአንጻሩ ቦሌ ክፍለ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።