ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ዛሬ 12ኛ ቀኑን ይዟል።
የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
በምድብ አንድ ኢትዮጵያ ከኬንያ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱ ሀገራት አስቀድመው ለግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ካሸነፈች ወይም በአቻ ምድቡን በመሪነት ታጠናቅቃለች።
በዚሁ ምድብ ደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከምድቡ የወደቁት ደቡብ ሱዳን በአንድ ነጥብ አራተኛ እና ሩዋንዳ ያለ ምንም ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በምድብ ሁለት ዩጋንዳ ከጅቡቲ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከሶስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ያገኘችው ዩጋንዳ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ጅቡቲ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።
ዩጋንዳ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፏ ይታወቃል። ጅቡቲ አስቀድማ ከምድቡ መውደቋ ይታወቃል።
በዚሁ ምድብ ሱዳን እና ብሩንዲ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሱዳን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃን ይዛለች። ብሩንዲ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ታንዛንያ በ12 ነጥብ ከምድቡ አስቀድማ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፏ ይታወቃል።