ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከመቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከመርሃ ግብሮቹ መካከል መቻል ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ካከናወናቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። 

ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

መቻል የሊጉ መሪ ለመሆን፣ ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ለማጠናከር ይጫወታሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከፋሲል ከነማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሃዋሳ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው  አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።  9 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ አራት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ13 ነጥብ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ በሊጉ ስድስት ጨዋታዎችን በማድረግ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር የተቆጠረበት አንድ ጎል ብቻ ነው። 

ፋሲል ከነማ በ12 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በ11 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

ሸገር ከተማ በሊጉ ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በስምንት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ኢትዮጵያ ቡና በአራት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም