ቀጥታ፡

ቼልሲ ባርሴሎናን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦  በአውሮፓ ሻምፒዮስ ሊግ ተጠባቂ መርሃ ግብር ቼልሲ ባርሴሎናን 3 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ እስቴቫኦ፣ ሊያም ዴላፕ እና የባርሴሎናው ጁል ኩንዴ በራሱ ግብ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የባርሴሎናው አምበል ሮናልድ አራውሆ በ44ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

የአራውሆ መውጣት የባርሴሎና ጨዋታ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። በአንጻሩ ቼልሲ የቁጥር ብልጫውን በሚገባ ተጠቅሟል።

በኢትሃድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባየር ሌቨርኩሰን ማንችስተር ሲቲን  ባልተጠበቀ ሁኔታ 2 ለ 0 አሸንፏል።

አሌሃንድሮ ግሪማልዶ እና ፓትሪክ ሺክ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ወደ ቬሎድሮም ስታዲየም ያመራው ኒውካስትል ዩናይትድ በማርሴይ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል። ፒዬር-ኤሜሪክ ኦቦሜያንግ ለፈረንሳዩ ቡድን ግቦቹን አስቆጥሯል።

ሃርቪ ባርንስ ለኒውካስትል ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ቪያሪያልን 4 ለ 0 አሸንፏል። ሴርሁ ጉይራሲ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ካሪም አዲዬሚ እና ዳንኤል ስቬንሰን ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ጉይራሲ በጨዋታው ቡድኑ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የቪያሪያሉ ሁዋን ፎይዝ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ናፖሊ ካራባግን 2 ለ 0 አሸንፏል። ስኮት ማክቶሚናይ እና የካራባጉ ማርኮ ያንኮቪች በራሱ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ጁቬንቱስ ቦዶ ግሊምትን 3 ለ 2 አሸንፏል።

የስላቪያ ፕራግ እና አትሌቲኮ ቢልባኦ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ቤኔፊካ አያክስን 2 ለ 0፣ ሴይንት ዩኒየን ጊሎይስ ጋላታሳራይን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም