ቀጥታ፡

የሆርቲካልቸር ምርቶች ለግብርናው ሁለንተናዊ  እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦የአትክልት፣ፍራፍሬ እና አበባ ( ሆርቲካልቸር) ምርቶች ለግብርናው ሁለንተናዊ  እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት ሆርቲ ላይፍ ለርኒንግ በተሰኘ መርኃ ግብር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እ. ኤ. አ ከ2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ እየሰራ ይገኛል፡፡

የድርጅቱን ውጤታማ ተሞክሮና ስኬቶች ወደ ሁሉም ክልሎች ለማስፋት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የግብርና ሚኒስቴርና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡


 

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ፤ የአትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ ( ሆርቲካልቸር) ምርቶች ለግብርናው ሁለንተናዊ  እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል፡፡

አትክልትና ፍራፍሬ ለምግብና ስርዓተ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንዲሁም ለአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአረንጓዴ አሻራና ለኢኮኖሚ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል ፡፡  

የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንዲሁም በአርሶ አደሩ ግብዓት አጠቃቀምና የግብርና ስራ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ ስልጠናዎች እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ፡፡

በስልጠናው በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው ተሞክሮውን ወደ ሁሉም ክልሎች ማስፋፋት  በሚቻልበት ጉዳይ ዙርያ ለመምከር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል  ፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪና የልማት ኮርፖሬሽን መሪ ፓውላ ሽናድለር፤ ድርጅቱ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት እንዲያድግ  በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


 

በመድረኩ የተገኙት አርሶ አደር መጣዓለም ፋንታሁን፤ በአትክልትና ፍራፍሬ አመራረት ዙሪያ በድርጅቱ አማካኝነት ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውሰዋል፡።


 

በስልጠናው በመታገዝ አቮካዶ ፣ብርቱካን፣ ፓፓያና ማንጎ እያመረቱ እንደሚገኝ በመጥቀስ አሁን ላይ ለሎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

በወሰዱት ስልጠና በትንሽ መሬት ብዙ ምርት ማምረት በመቻላቸው በአካባቢያቸው ለሚገኙ አርሶ አደሮች አርአያ ለመሆን መብቃታቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ቀኑብሽ የሱፍ  ናቸው ፡፡


 

የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት በሰባት ክልሎች በሚገኙ 200 ወረዳዎች 2 ሺህ 144 ተጠቃሚዎችን በመያዝ  31 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረጉ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም