የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር የክስተት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር የክስተት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ የማርበርግ ቫይረስን በራስ አቅም መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል በማቋቋምና የክስተት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማርበርግ ቫይረስ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሀገራት የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ከተማ የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ ከታማሚ ሰው ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚኖር ቀጥታ ንክኪ የሚተላለፍ መሆኑንም አንስተዋል።
በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምልክቶች ትኩሳት፣ የሰውነት መቆረጣጠም፣ ደም መፍሰስ መሆናቸውን ጠቁመው፤ መሰል ምልክቶች የታዩበት ሰው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የሚመራ ሀገር አቀፍ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ ግብረ ኃይሉ በየቀኑ በሽታው ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ግምገማ እያካሄደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሀገር አቀፍ የክስተት አስተዳደር ሥርዓት ተዘርግቶ የቅንጅትና የማስተባበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የማከም፣ ቅኝትና ልየታ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርመራ የሚደረግበት ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ወደ ጂንካ ተልኮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህክምና የሚያስፈልጉ የሎጂስቲክስ አቅርቦት ተደራሽ መደረጉንም ገልፀዋል።
በሽታውን ለመከላከል ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ኮቪድ-19 በተከሰተበት ወቅት ዝግጅት ላይ መስራት ከምላሽ ስራ ይልቅ ውጤታማ እንደሚያደርግ ግንዛቤ በመወሰዱና ልምድ በመቀሰሙ የሰው ኃይል ስልጠና፣ የህክምና ተቋማትን የማስፋፋትና አቅማቸውን የማሳደግ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተከታታይነት ያለው መረጃን በመስጠት የተግባቦት ስራን ለማጠናከር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ ከሚመለከታቸው አካላት ብቻ የሚወጡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር በሽታውን መከላከል እንዳለበት ገልፀዋል።
ጥያቄ ያላው ሰው በነፃ የስልክ መስመር 8335 አሊያም 952 በመደወል በማንኛውም ሰዓት አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት እንደሚችልም ነው የጠቆሙት።
እስከትናንት ባለው መረጃ አስር ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል አምስቱ በጤና ተቋም ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።