ቀጥታ፡

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በጋራ መስራት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አዲስ ከተካተቱ ተቋማት መሪዎችና ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ላይ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ማህበራት እና የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።

ከዚህ በፊት ከነበሩ አባላት በተጨማሪ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራት አመራር አባላት በምክር ቤቱ እንዲካተቱ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።

የአይበገሬነት አስተሳሰብ በመገንባት ከተረጂነት አመለካከት ለመላቀቅና በራስ አቅም ለመደጋገፍ በተለይ የምክር ቤቱ አባላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በራስ አቅም ለአደጋ ምላሽ የመስጠት አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጉዳይ ከብሔራዊ ደህንነት አጀንዳ፣ ከማህበራዊ ዋስትና፣ ከዘላቂ ልማትና ሰላም ማስፈን ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲና አዋጅ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፍን የተቋማት ተሳትፎና ሚናቸውን እንዲወጡ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የምክር ቤቱ አባላት እንደገለጹት፤ በራስ አቅም የሚከናወን የሰብዓዊ እርዳታ ምላሽ አሰጣጥ ለሉዓላዊነት መከበር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።


 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት፤ በሃይማኖት ተቋማት በተናጠል የሚደረጉ እርዳታዎች በቅንጅት ስራ ላይ ቢውሉ ለሰብዓዊ ምላሽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።

ኮሚሽኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ማሳተፉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሓፊ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ኮሚሽኑ የያዛቸው እቅዶች እንዲሳኩ ባሉት መዋቅሮች በመታገዝ ትብብሩን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።


 

መንግስት ጠባቂነትን በማስቀረት ለአደጋ ስጋት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የያዘው አቋም ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲቪል ማህበረሰብ ፎረም ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሳይ ደረጀ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማቀናጀት ለአደጋ ስጋት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።


 

ፎረሙ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግና በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም