ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ብትወጣ የበለጠ ለቀጣናው ሠላም ትሠራለች

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ብትወጣ የበለጠ ለቀጣናው ሠላም ትሠራለች ሲሉ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን ገለጹ።

አዛዡ ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን የተመራ ልዑክ ከኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ዛሬ ባደረጉት ውይይት በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የቀጣናው ሀገራት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።


 

በውይይቱ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊውን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ለበርካታ ዓመታት በትብብር እየሠሩ መምጣታቸውን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ አልሸባብን ለማዳከምና የሽብር ሴራውን ለማክሸፍ የምትወስደውን የኃይል እርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው የባሕር በር ፍላጎቷም ለሠላማዊና ኢኮኖሚዋን ለመገንባት መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ፀጥታን ለማስፈን እየተጫወተች ያለችውን ሚና ያደነቁት የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን ሽብርተኝነትን በጋራ የመዋጋት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የገለፁት የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዡ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ብትወጣ የበለጠ ለቀጣናው ሠላም ትሠራለች ብለው እንደሚያምኑም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ፍላጎቶችንና በቀጣናው ሠላምን ለማረጋገጥ ስለያዘቻቸው ዕቅዶች ከዋሺንግተን ዲሲ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩም ጠቁመዋል።

በዕለቱ "የአፍሪካ ቀንድ የሠላም ሁኔታ" በሚል ርዕስ በኮሎኔል መስፍን አውላቸው ጥናታዊ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል።

ከውይይቱ በተጨማሪ ሁለቱ ሀገራት ስጦታ መለዋወጣችውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ የላከው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም