ቀጥታ፡

በክልሉ የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

ሆሳዕና ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች የብዙዎችን ህይወት እየለወጡና ተጠቃሚም እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

በስልጠና ላይ የሚገኙ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በክልሉ የከተማና ገጠር ኮሪደር ስራዎችን እንዲሁም የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

በክልሉ የተከናወኑ የተለያዩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች የብዙዎችን ህይወት እየለወጡ እና ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ብሩክ ቡናሮ በገጠርና ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች በተጨባጭ ዜጎችን እየጠቀሙ መሆኑን ለማየት ችለናል ብለዋል።


 

በግብርና ልማት፣ አገልግሎት አሰጣጥና ዘመናዊ አሰራርን ከመዘርጋት አንፃር የተከናወኑ ተግባራትም እመርታዊ ለውጥ የታየባቸው መሆኑን አንስተዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊ ወይዘሮ አስቴር ይርዳ፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎችም የዲጅታል አገልግሎቶች ተግባራዊ መደረጋቸው መሰረታዊ የአገልግሎት ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።


 

በዲጅታል አገልግሎት አሰጣጥ የብልሹ አሰራር መንገዶችን በመዝጋት፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም እንግልትን ማስቀረት ስለመቻሉ አንስተዋል።

በገጠር የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ የሚቀይሩ እና ዘመናዊነትን የሚያላብሱ በመሆናቸው የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አመራር ሲቲ ሙስጠፋ ናቸው።


 

የከተሞች የኮሪደር ልማት ዘመናዊና ስማርት ሲቲ በመገንባት እንዲሁም ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

በጉብኝታቸው የተከናወኑ ስራዎችን በተግባር ከመመልከትም ባለፈ ለቀጣይ ስራዎች ልምድና ተሞክሮ ያገኙበት መሆኑን አመራሮቹ አረጋግጠዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ መሎ፤ የመስክ ጉብኝቱ ዓላማ አመራሮቹ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን በተግባር እንዲመለከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በየአካባቢው የተሰሩ እና በግንባታ ላይ ያሉ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ለላቀ ስራ ልምድና ተሞከሮ ያገኙበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም