የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የነፃ ንግድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን አቅም ለመጠቀም ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የነፃ ንግድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን አቅም ለመጠቀም ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የነፃ ንግድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን አቅም ለመጠቀም እንደሚያስችል ተመላከተ።
ነፃ የንግድ ቀጣናው የኢንዱስትሪ ልማትን፣ የኢኮኖሚ ብዝሃነትንና ዘላቂ ልማትን የሚያበረታታ እንዲሁም የገበያ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ፖሊሲና ደንቦችን ማጣጣምና የኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አተገባበር ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ እንደገለጹት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ስር ካሉት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የነፃ ንግድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን አቅም ለመጠቀም ያስችላታል ብለዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣናው የኢንዱስትሪ ልማትን፣ የኢኮኖሚ ብዝሃነትን እና ዘላቂ ልማትን የሚያበረታታና የገበያ ትስስርን የሚያጠናከር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ቀጣናው ለአፍሪካ ሀገራት እኩል የንግድ ዕድሎችን የሚያስገኝ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ሀገር የሚያገኘው ጥቅም የሚወሰነው ተወዳዳሪ የሆኑ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በማምረት እና ገበያን በብቃት በመጠቀም ነው ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንዱስትሪ ሽግግር፣ ለአካታች የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡
የኢንተርፕራይዞቹን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የነፃ ንግድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን አቅም ለመጠቀም ያስችላታል ሲሉም ተናግረዋል።
መንግሥት ምርታማነትን በሚያሳድጉ የተለያዩ ፕሮግራሞች በመታገዝ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱን እንደ ንግድ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ለውጥ እንደትልቅ ዕድል እንደምትመለከተው ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ለማሻሻል ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማጠናከር አማራጭ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ በትኩረት መስራት በነፃ ንግድ ቀጣናው ያለውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመድረኩ የቀረበው ጥናት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋት ከአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና በአግባቡ በመጠቀም የኢኮኖሚ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን ያስቀመጠ ነው ብለዋል።