ቀጥታ፡

በቡና ወጪ ንግድ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ ስኬት የቡና አምራች ዜጎችን ተስፋ አለምልሟል 

አዲስ አበባ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ከአራት ዓመታት ወዲህ በቡና ወጪ ንግድ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ ስኬት የቡና አምራች ዜጎችን ተስፋ ያለመለመ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለ2017 እቅድ አፈጻጸም መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የእውቅና መርኃ ግብር አከናውኗል።


 

በመርኃ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ቡና አምራቾችና ላኪዎች የተገኙ ሲሆን በቡና ወጪ ንግድ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ላኪዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉ የቡና ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ አነቃቅቷል ብለዋል።

ከአራት ዓመታት ወዲህ በቡና ወጪ ንግድ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ ስኬት የቡና አምራች ዜጎችን ተስፋ እያለመለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በ2017 በጀት ዓመትም የተመዘገበው የቡና ወጪ ንግድ ስኬት መንግሥት ከምርት እስከ ገበያ በወሰዳቸው እርምጃዎች በአርሶ አደሮችና በዘርፉ ባለድርሻ አካላት ትጋት የተገኘ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ የተመዘገበው ገቢም የኢትዮጵያ ክብረወሰን መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ቀጣይነት ያለው የገበያ መዳረሻ የማስፋት ስራ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ጊዜውን የዋጀ የግብይት ስርዓት ለነገ የማይባል ቁልፍ ስራ መሆኑን ጠቁመው፤ የቡና ሜካናይዜሽን እርሻን ማስፋትና ቡና ላይ እሴት ጨምሮ መላክ የትኩረት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ያላቸው የቡና ዝርያዎች ባለቤት መሆኗን ጠቁመዋል።


 

ከለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ መጨመሩን ጠቅሰው፥ በ2017 በጀት ዓመት 470ሺህ ቶን ቡና በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ታሪካዊ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።

በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ በማምጣትና የቡና ምርትና ግብይት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የተገኘ ስኬት መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ቡና የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ጥራታቸው አስተማማኝና ተመራጭ የሆኑ የቡናና ሻይ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም