በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ወልቂጤ ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ 2ተኛ ዙር ሰልጣኝ አመራሮች በጉራጌ ዞን የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
ሰልጣኝ አመራሮቹ በዞኑ የተከናወኑ የሌማት ትሩፋት፣ የግብርናና ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የጎበኙ ሲሆን የተከናወኑ ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሙሉቀን ገዙ፣ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የጀመራቸው ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ጊዜ፣ ጉልበትንና በጀት የሚቀንሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የጀመራቸው ስራዎች የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አሰለፈች ለማ በበኩላቸው፤ በወልቂጤ ከተማ በሁሉም መስኮች እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን አድንቀዋል።
በየአካባቢው እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ጀምሮ የመጨረስ አቅም እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ ናቸው ያሉት ደግሞ አቶ በህሩ ኸይረዲን ናቸው።
ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍና የከተማ ግብርና ላይ ስኬታማ ስራዎች መመልከታቸውን ገልጸው የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አመራሩ ፍጥነት የታከለበት ስራ ማከናወን አለበት ብለዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር፣ በከተማው የተጀመሩ የለውጡ ትሩፋቶች ለህዝቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማው የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት፣ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎትና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ፍጥነትንና ፈጠራን በማከል በውጤታማነት እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም በቱሪዝም፣ በግብርና ልማትና በሌሎች ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል ፡፡
ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው አመራር በሚወስደው ስልጠና የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን አጎልብቶ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
አመራሮቹ ባለፉት ቀናት የወሰዱት ስልጠና አቅማቸውና ክህሎታቸውን በማሳደግ በፍጥነት እና በጥራት የማስፈፀም አቅማቸውንም እንዳጎለበተውም ተናግረዋል፡፡