በባሌ ዞን እየተተገበረ የሚገኘው የጤና መድህን ስርዓት ልምድ የሚወሰድበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን እየተተገበረ የሚገኘው የጤና መድህን ስርዓት ልምድ የሚወሰድበት ነው
ሮቤ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን እየተተገበረ የሚገኘው የጤና መድህን ስርዓት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑ ተገለጸ።
ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት እና ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ተቋማት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች የባሌ ዞን የአንድ ቋት የጤና መድህን አሰራርን በመጎብኘት ልምድ ቀስመዋል።
በልምድ ልውውጥ መድረኩ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተርና የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ያምሮት አንዷላም ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግሥት አካታችና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት የቀረፀው የጤና መድህን ስርዓት የሚታይ ውጤት እያስመዘገበ ነው።
በተለይም ዜጎች የጤና መድህን አባል በመሆን ዓመቱን ሙሉ እንዲታከሙ የተመቻቸው ሁኔታ በገንዘብ እጦት ምክንያት ዜጎች የጤና እክል እንዳያጋጥማቸው እየደገፈ መሆኑን በመስክ ምልከታ ጭምር ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በዞኑ ከጤና መድህን አባላት በዓመት አንዴ ብቻ ገንዘብ በአንድ ቋት በማሰባሰብ ዓመቱን ሙሉ ሳይጉላሉ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አክለዋል።
በዚህም በስርዓቱ አልፎ አልፎ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትና በየጤና ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የመድኃኒት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳሚኖረው አመልክተዋል።
የባሌ ዞን አብዛኛው ነዋሪ የጤና መድህን አባል በመሆን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገበት ሁኔታ በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና ባለሙያ አቶ ቸርነት መንግሥቴ ናቸው።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የጤና መድህን ተጠቃሚ አባላት መረጃን ወደ ዲጂታል ቋት በማስገባት ተጠቃሚው ሳይጉላላ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉ ሌላው በመስክ ምልከታቸው ከተመለከቱት መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
ከአባላት ድጎማ የተሰበሰበን ገንዘብ በዞኑ ቋት ገቢ በማድረግ አባላቱ በየደረጃው በሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ሳይጉላሉ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ ሌላው በተሞክሮነት ከወሰዱት መካከል እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዞኑ ከ763 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች የጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘገየ ዘውዴ ናቸው።
የአንድ ቋት አገልግሎቱ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ይነሳ የነበረውን የተጠቃሚዎች ቅሬታ በመፍታት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ያስቻለ በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፤ በዞኑ በጤናው ዘርፍ በተወሰኑ ወረዳዎች የታዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ወደ ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የጤና መድህን ስርዓት የታቀፉ ዜጎች ቁጥር 30 ነጥብ 1 ሚሊዮን መድረሱን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የኃብት አሰባሰብና የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ዲንቃ ኢረና ናቸው።
በተለይም በባሌ ዞን ለጤና መድህን አገልግሎት ከአባላቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ በአንድ ቋት የማሰባሰብ የአሰራር ሂደት ወደ ሌሎች ዞኖች እንዲሰፋ በማድረግ የጤና መድህን አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።