የቆየውን የአብሮነት እሴት በህብረ ብሔራዊ አንድነት መርህ አጠናክረን እናስቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የቆየውን የአብሮነት እሴት በህብረ ብሔራዊ አንድነት መርህ አጠናክረን እናስቀጥላለን
ሚዛን አማን፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦የቆየውን የአብሮነት እሴት በህብረ ብሔራዊ አንድነት መርህ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በዞኑ ሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች የቆየውን የአብሮነት እሴት በህብረ-ብሔራዊ አንድነት መርህ አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዋሲሁን ገብረሚካኤል በሰጡት አስተያየት፤ ሕገ መንግሥቱ የሁላችን ማንነት፣ ታሪክና ባህል እንዲከበር የሰጠውን መብት ይዘን የጋራ ተጠቃሚነታችንን በሚያረጋግጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ለትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት ትኩረት በመስጠት መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ብርቅነሽ ኃይሉ በበኩላቸው፤ በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ውበታችንን ለዓለም የምንገልጽበትን አጋጣሚ የፈጠረልን በመሆኑ በልዩ ሁኔታ እናከብረዋለን ሲሉም ተናግረዋል።
በዓሉ አንዱ የአንዱን ባህላዊ ማንነት የሚረዳበትና ኢትዮጵያዊ ቀለምን በኅብረ ብሔራዊነት የምናደምቅበትን ዕድልን የሚፈጥር ነው ያለው ደግሞ ወጣት ኤርሚያስ ጣባ ነው።
ኢትዮጵያ በብዝኃ ማንነት በተባበረ ክንድ ትላልቅ ድሎችን እየተቀዳጀች ወደ ፊት ትቀጥላለች ያለው ወጣት ኤርሚያስ የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለጋራ ልማት መትጋት ይኖርብናል ብሏል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ ተካልኝ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት በሀገራዊ ጥቅሞቻችን ላይ በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዞኑ ወረዳዎች ሰው ተኮር ተግባራትን በመፈጸም መከበሩን ጠቅሰው ያለምንም ልዩነት የመተጋገዝና የመረዳዳት ልምድን አዳብሮ ለመቀጠል የሚያስችል ሥራ እንደተሰራም አመልክተዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መስፍን መንገሻ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ብሔረሰቦች ተዋደውና ተከባብረው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በጋራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለአካባቢው ዕድገትና ሰላም መስፈን ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።