ቀጥታ፡

ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታና ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሚናችንን እናጠናክራለን - የተፎካካሪ ፓርቲዎች

ጎንደር፤ ህዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታና ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ በጎንደር ከተማና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አመለከቱ፡፡

''የማህበረሰቡን የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም በመጠበቅ ረገድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና'' በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ካሳ በለጠ እንዳሉት ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ልንሰራ ይገባል፡፡

በተጨማሪም ለሀገር ልማትና ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መዳበርም መትጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተሳሳተ ትርክትን ማረም ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ ሌላኛው የጋራ ምክር ቤቱ አባል መኮንን ብርሃን ናቸው።

ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ አባል ስፋ መኮንን በበኩላቸው አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአሮጌው የፖለቲካ ባህል በመላቀቅ በትብብርና በመደማመጥ መርህ ለሰላም መስፈን በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተገኑ ደረጀ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫና የምክክር ኮሚሽን ተልዕኮ እንዲሳካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መስፈን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ለስኬቱ ሲያደርጉ የቆዩትን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።

በጋራ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በጎንደር ከተማና በማእከላዊ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ 10 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም