በነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምናው እይታችን በመመለሱ ተደስተናል - ኢዜአ አማርኛ
በነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምናው እይታችን በመመለሱ ተደስተናል
ነገሌ ቦረና፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦በነገሌ ቦረና ሆስፒታል በተደረገላቸው ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና እይታቸው በመመለሱ በእለት ተእለት ህይወታቸው ሲያጋጥማቸው የቆየውን ችግር እንደሚቀንስላቸው ታካሚዎች ገለጹ።
በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በጎ ፈቃደኛ ሀኪሞች ቡድን የአይን ሞራ ግርዶሽ የህክምና አገልግሎት ትናንት በነገሌ ቦረና ሆስፒታል ተጀምሯል፡፡
በዞኑ ሊበን ወረዳ የአርዶት ቀበሌ ነዋሪ አቶ አደም ቢዶ፤ በአይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ከስራና ከማህበራዊ ህይወት ተገልለው አንድ አመት ቤት መዋላቸውን አስታውሰዋል፡፡
ህክምናውን ለማድረግም አቅም በማጣታቸው ተቸግረው በነበሩበት ወቅት የነጌሌ ቦረና ሆስፒታል ነጻ ህክምና አገልግሎት ስለሰጣቸው ተደስተዋል።
ያገኙት ህክምናም በእለት ተእለት ህይወታቸው ሲያጋጥማቸው የቆየውን ችግር እንደሚቀንስላቸው ተስፋ አድርገዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው ሀጂ አብዱልቃድር ኢብራሂም፣ በአይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ማየት ተስኗቸው አራት አመታትን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
አይናቸውን ለመታከም በአቅራቢያቸው ባሉ ህክምና ተቋማት ቢሞክሩም መዳን እንዳልቻሉ ጠቅሰው አሁን ላይ በሆስፒታል በተደረገላቸው ህክምና ዳግም ማየት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ፈውስ ማግኘታቸውን የሚመሰክሩት ደግሞ ወይዘሮ አያልነሽ ጫኔ ናቸው።
በተደረገላቸው ህክምና በቀጣይ ህይወታቸውን ያለአጋዠ ለመምራት ስላበቋቸው የህክምና ቡዱን አባላቱን አመስግነዋል።
የአርባምንጭ ሆስፒታል ነጻ የአይን ግርዶሽ ህክምና ቡድን መሪ አቶ ደመቀ ደበበ፤ የአይን ህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎችን ይዘው ወደ ነገሌ ቦረና ሆስፒታል መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
በነገሌ ቦረና ሆስፒታል በሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ለ500 ሰው ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ለመስጠት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
የነገሌ ቦረና ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ቦነያ ሊበን በበኩላቸው፤ የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ለማግኘት ከተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ነዋሪዎች ወደ ነገሌ ቦረና ሆስፒታል እንደሚመጡ ጠቅሰዋል፡፡
ከነጻ ቀዶ ህክምናው ጎን ለጎንም የግልና የአካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ የአይን በሽታን መከላከል የሚቻልበት ሂደት ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።