ቀጥታ፡

ውድድሩ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ማፍራትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ሀገር አቀፍ የፈጠራ ሀሳቦች ውድድር ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ማፍራትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

ብሩህ ኢትዮጵያ የ2018 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የቢዝነስ ፈጠራ ውድድር ስልጠና በቢሾፍቱ ተጀምሯል።

"ማሰልጠን መሸለም ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የዘንድሮው ስድስተኛ ዙር የፈጠራ ውድድር ከመላ ኢትዮጵያ የተወጣቱ 251 የፈጠራ ባለቤቶች ተሳትፈውበታል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዓለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት ይቀያየራሉ።

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ፈጠራና ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ ለፈጠራና ኢንተርፕረነርሽፕ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ለማጎልበትና የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ለማዳበር ባለፉት አምስት ዓመታት የብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳብ ውድድር መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የአዳዲስ ሀሳቦች ማመንጫ ማዕከላት እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክህሎትን ማሳደግ የስልጠናችን ማጠንጠኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ፈጠራና ኢንተርፕረነርሽፕ ችግር ፈቺ ውጤቶችን ለማፍለቅ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዙር የብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳቦች ውድድር ከ12 ሺህ 500 በላይ ሀሳቦች ለውድድር መቅረባቸውን ገልጸዋል።

በየውድድሩ የተሻለ የፈጠራ አቅም ያሳዩ ከአንድ ሺህ 300 በላይ ሀሳቦች የተሸለሙ ሲሆን 580ዎቹ ወደ ስታርትአፕ በመሸጋገር ከ30 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በዘንድሮው ውድድር የላቀ የፈጠራ ሀሳብ በማቅረብ የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎችን ከባንክ ጋር በማስተሳሰር ካምፓኒ መመስረት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ነው ያሉት።

የፈጠራ ሀሳብ ተወዳዳሪዎች የኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የፈጠራ ሀሳቦች ውድድር ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ማፍራትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች ለኢትዮጵያ ከፍታና ልዕልና አምባሳደር የሚሆን ተቋም መገንባት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የፈጠራ ስራቸውን ወደ ምርት ለማስገባት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ስልጠናው የፈጠራ ስራዎችን ማላቅ የሚያስችል ዕውቀትና ጥበብ የሚፈራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር)፥ የፈጠራ ሀሳብ ተወዳዳሪዎች ከወረዳ ጀምሮ የተሻለ የፈጠራ ሀሳብ አቅርበው አሸንፈው የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገር አቀፍ የፈጠራ ሀሳብ ውድድርና ስልጠናው የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ መሬት ለማውረድ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች ምድር ናት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አቅማቸውን እንዲያጉለብቱ ማሰልጠንና ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ወጣቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን የሚያጎለብቱበት ስልጠና መስጠቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም