ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ የምትከተለው የዕድገት መርህ አረንጓዴ የዕድገት አቅጣጫን መሠረት ያደረገ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ የምትከተለው የዕድገት መርህ አረንጓዴ የዕድገት አቅጣጫን መሠረት ያደረገ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ የምትከተለው የዕድገት መርህ አረንጓዴ የዕድገት አቅጣጫን መሠረት ያደረገ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒትሩ፥ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።
በዚህም ወቅት፥ የለውጡ መንግሥት በግብርና ዘርፍ ለቡና ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረትና በዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ባለፉት ዓመታት አስደማሚ ለውጦችን አስመዝግበናል ብለዋል።
ምርታማነት በእጅጉ ጨምሯል፤ ቡና አምራች አርሶ አደሮቻችንም በቡና ልማት ተስፋ ከመቁረጥ ወጥተው ዛሬ ላይ ሚሊየነር እየሆኑ እንገሚገኙ ገልጸው፥ በ2017 በጀት ዓመት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፥ ይህ ውጤት በምርት መጠንም ሆነ በገቢ አዲስ ታሪክ የተጻፈበት ነው ያሉት።
በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት የያዝነውን ግብ ለማሳካት ጥራትን ማሻሻልና ቡናን እሴት በመጨመር ወደ ውጭ መላክ ትኩረቶች መሆናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ግንባር ቀደም የቡና፣ የሻይና የቅምማ ቅመም አምራች ለማድረግ በፍጥነትና በጥራት መርህ የጋራ ጥረትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።