ኢትዮጵያ የአህጉሪቷን ዕድገትና ብልጽግና የሚያሳልጥ ፓን አፍሪካ የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአህጉሪቷን ዕድገትና ብልጽግና የሚያሳልጥ ፓን አፍሪካ የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዕድገትና ብልጽግና የሚያሳልጥ ፓን አፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እየገነባች መሆኗን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ገለጹ።
"የአቪዬሽን ስልጠና፥ ለኢንዱስትሪው ዕድገት፣ ፈጠራ፣ ብርታትና ዘላቂነት አንቀሳቃሽ" በሚል መሪ ሃሳብ አምስተኛው የአፍሪካ አቪየሽን ማሰልጠኛ ተቋማት ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንና በአፍሪካ የአቪዬሽን ስልጠና ድርጅቶች ማኅበር ትብብር የተዘጋጀው ጉባኤ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ተገልጿል።
በዚሁ ጊዜ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፤ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሀገራት መካከል ያለውን ንግድና ቱሪዝምን የሚያሳልጥ ወሳኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው ብለዋል።
የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት በማሳለጥ የሀገራትን የንግድ፣ ቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብርን በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ስኬታማ የበረራ ተሞክሮና ቀጣይ ዕቅድ የአፍሪካን የጋራ ብልጽግና ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፍና ስኬታማ ከመሆን ባለፈ በረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት እቅድና ሙያዊ ብቃት እየተመራ የሚገኝ የፓን አፍሪካዊ ተቋም ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትና የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በሙሉ አቅም ተግባራዊ ሲደረጉ የአህጉሪቱን የሥራ ዕድል ፈጠራና ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽሉት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2035 የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በያዘው ግዙፍ ርዕይ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ማስጀመሩን አስረድተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን የትራንስፖርት እና ሞቢሊቲ ኃላፊ ኤሪክ ንታጌንጌርዋ፤ የአፍሪካን አህጉራዊ የልማትና ትስስር ተነሳሽነት በሚገባ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የህዝቦችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአየር ትራንስፖርት ዕቅዶችን ለመተግበር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተወካይ ጌታቸው ቢያ፥ የሰው ሃብት ልማት፣ ትምህርትና ስልጠና ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት መሰረት ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለትምህርትና ስልጠና የሰጠው ትኩረት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን እያሳደጉለት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የአፍሪካ አቪዬሽን ማሰልጠኛ ተቋማት ማኅበር ፕሬዝዳንት ተንዳኔ ናዶ፣ የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ትስስር በማሳደግ ብቃት ያለው የሰው ሃብት ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያና የአባል ሀገራት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተቋማት ለማኅበሩ ዕድገት ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።