ቀጥታ፡

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር ዝግጅቱን አጠናቀቀ

ባህር ዳር፤ ህዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገለፁ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የገቢ ምንጮች በማስፋትና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻልን ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመደንገግ የወጣው አዋጅ 1294/2015 ያመለክታል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሻለ አካዳሚያዊ፣ የፋይናንስና አስተዳደር ነፃነት ኖሯቸው ለትምህርት ጥራት እንዲሰሩ ራስ ገዝ መሆናቸው መልካም ጅማሮ መሆኑ በብዙ ተመክሮበታል።

በዚህም ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አሥሩ ራስ ገዝ እንዲሆኑ የማድረግ ጥረት የቀጠለ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሆኖ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በራስ ገዝነት እንዲካተቱ መደረጉ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን በተሻለ ደረጃ ማከናወን የሚያስችላቸው መሆኑን አንስተው፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አካቶ እየሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ከሀገሪቷ አቅምና ገበያውን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ለማፍራት የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለዚህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በምርምርም ሆነ መማር ማስተማር እንዲሁም በቴክኖሎጂ ፈጠራና በማህበረሰብ አገልግሎት ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ስምሪት፣ ሃብት የማመንጨት አቅም፣ አስተዳደራዊ መዋቅርና መሰል ተግባራትን በማካተት ውስጣዊ ግምገማ በማድረግ ውጤቱን ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩን ገልፀዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው ፈቃድ መሰረት ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝነት አሰራሩን ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ በመሆን የመማር ማስተማር ስራውን በማከናወን ላይ መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም