ቀጥታ፡

በአርሲ ዞን የቀበሌ አደረጃጀትን ለማጠናከር ከ500 በላይ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ተገንብተዋል

አዳማ፤16/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን የቀበሌ አደረጃጀትን ለማጠናከር ከ500 በላይ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በዞኑ አዲስ የተዘረጋው የቀበሌ መዋቅር እንዲጠናከር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የቀበሌ መዋቅሮቹ ለህበረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሰው ኃይል የማሟላት እና የተሻለ ጽህፈት ቤቶች እንዲኖራቸው እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት መዋቅሩ ከተዘረጋ ወዲህ በዞኑ ከተደራጁ 580 ቀበሌዎች ውስጥ 564 ለሚሆኑት ጽሕፈት ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በቀበሌ ጽህፈት ቤቶች አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብም የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተሟሉላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የሰው ኃይልን ከማሟላት ባለፈ ወደ ቀበሌ መዋቅር የተመደቡ አመራሮችም ተረጋግተው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የመኖሪያ ቤት እየተገነባ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የቀበሌ መዋቅሩ ከተዘረጋ ወዲህ የህብረተሰቡ የፍትህ፣የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ረገድም አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው ብለዋል።

በዚህም በአብዛኛው የዞኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ህብረተሰቡ ትኩረቱን ልማት ላይ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።

በዞኑ ሄጦሳ ወረዳ ሻቂ ሸረራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈይሣ ቡታ፣ የቀበሌ አስተዳደር በአካባቢያቸው በመደራጀቱ የተሻለ አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በቀበሌ መዋቅሩ የተመደቡ አመራሮችም ተገልጋዩ ያለበት ቦታ ድረስ በመውረድ መሰረታዊ አገልግሎት እየሰጧቸው መሆኑንም አውስተዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወረዳ ድረስ ይመላለሱ እንደነበር አንስተው አዲስ የተዘረጋው የቀበሌ መዋቅር በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ቦታ ለማግኘት እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።

በወረዳው የኢተያ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታከለ ዳቢ፣ አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ትራንስፖርትን ጨምሮ ያወጡ የነበረውን አላስፈላጊ ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

በተለይም የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀበሌያቸው ድረስ እየቀረበላቸው በመሆኑ ለግብርና ልማት ስራቸው ትልቅ እገዛ ማድረጉን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም