ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 16/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት አዳማ ከተማ ከባህርዳር ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ ካካሄዳቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦች ተቆጥረውበታል።

ባህር ዳር ከተማ በዘጠኝ ነጥብ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ወላይታ ድቻ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። አራት ጊዜ ሲሸነፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በሁለት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ግቦችን አስተናግዷል።

ወልዋሎ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ መድን ከነጌሌ አርሲ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባካሄዳቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ግቦችን አስተናግዷል። 

መድን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በስምንት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ነጌሌ አርሲ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር በአምስት አጋጣሚዎች ግብ ተቆጥሮበታል።  አዲስ አዳጊው ቡድን በስድስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሕዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ13 ነጥብ እየመራ ነው።

መቀሌ 70 እንደርታ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ17ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም