ቀጥታ፡

መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የብዝሃ-ዘርፍ የኢኮኖሚ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን መደላድል ፈጥሯል

ድሬደዋ፣ ህዳር 15/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ጉዞ እንዲሳካ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ዛሬ ድሬ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

ኮሚሽነሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የዘመናት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ ይገኛል።

ከወረቀትና ከሰው ንክኪ የፀዱ አገልግሎቶች ተደራሽ መደረጋቸው ደግሞ ብልሹ አሠራሮችንና የሙስና ተግባራትን እንደሚቀንሱ ገልጸዋል።

ይበልጡኑ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎቶች ተደራሽ መሆናቸው እንደ አገር ለተጀመሩ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴዎች ዳር መድረስ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በድሬደዋ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዚሁ ጅምር ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ የተጀመረውን ስራ ለማሳደግ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፥ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በስፋትና በጥራት በመላው አገሪቷ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የድሬደዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐይር ሐጂ ኑር በበኩላቸው፥ በድሬ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት 10 ተቋማት 28 አገልግሎቶችን በጥራትና በፍጥነት ለተገልጋዮች ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች የተቀናጀ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰው፥ የተጀመረውን ስራ ለማስፋትና ለማሳደግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ዛሬ ረፋድ ላይ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማትንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም