ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለአምራቾች በተሰጠው ትኩረት በምርታማነትና በገበያ ማረጋጋት ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማነትን በማሳደግ የገበያ ማረጋጋት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር ገለጹ።

20ኛውን የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጀው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሺንና ባዛር ተከፍቷል።

ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ኤግዚቢሽንና ባዛር ገበያን የሚያረጋጉ የተለያዩ ምርቶች ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የለውጡ መንግሥት ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝምን የማጠናከርና ቀድሞ የነበሩ ጉድለቶችን የማረም ስራ ሰርቷል።

ይህም ዜጎች ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር አካባቢያቸውን ይበልጥ እንዲያለሙ ትልቅ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ ተሞክሮና ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

በራስ ምርት የመጠቀምና የመኩራት ባህል እንዲጎለብት እንዲሁም የኢትዮጵያን እንግዛ ንቅናቄን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የቀረቡ ምርቶች የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ትግበራ ፍሬ እያፈራ እንደሚገኝ የሚያመላክቱ፣ ገበያን የሚያረጋጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመዲናዋ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በተጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፥ ኢንዱስትሪዎቹ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የምርትና አገልግሎት ማሳያ፣መሸጫና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ መድረኮችን በማስፋት ለኢንዱስትሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፀጋዬ ደበሌ በበኩላቸው፥ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ 130 የሚሆኑ አምራቾች ምርታቸውን የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪዎች፣ በከተማ ግብርና የተሰማሩ አምራቾችና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የተሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ሸማቾችና አምራቾችን ቀጥታ በማገናኘት የዋጋ ንረትን መከላከልን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የተሳተፉ አምራቾች በሰጡት አስተያየት፥ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከኤግዚቢሽንና ባዛሩ በተጓዳኝ የደም ልገሳ መርሃ ግብርም ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም