ቀጥታ፡

አገልግሎቱ ለስደተኞችና ተመላሾች እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለስደተኞችና ተመላሾች እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

ቋሚ ኮሚቴው የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትን የ2018 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።


 

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ኃላፊ ጠይባ ሀሰን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ34 ሀገራት የመጡ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን በ27 መጠለያዎች ውስጥ እንደምታስተናግድ ገልጸዋል።

ተቋሙ የስደተኞችን አገልግሎት አሰጣጥ እና ደኅንነት ጥበቃ ሥራ ማጎልበት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት እውቅና መስጠትና ምዝገባ፣ ዶክመንቴሽን፣ የደኅንነት ስጋትን መቀነስና ዘላቂ መፍትሄ ላይ አበረታች ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የጤና እና ትምህርት አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ ለስደተኞች እና ተቀባይ ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ አገልግሎቱ ለበርካታ ስደተኞች እየሰጠ ያለው አገልግሎት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቀጣይም የሀገሪቱን ሠላምና ደኅንነት ባረጋገጠ መልኩ አገልግሎቱን ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ እየሰራ ያለውን ስራዎች አድንቀው፥ በቀጣይ በሀገሪቱ ላይ ጫናዎች እንዳይፈጠሩ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንዲሁም በማህበራዊ አገልግሎት በሆኑ የጤናና ትምህርት አገልግሎቶች ላይ ጫናዎች እንዳይፈጠሩ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱም አገልግሎቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም