ቀጥታ፡

አፍሪካ በአውሮፓ ገበያ ያላትን ተደራሽነት ለማሳደግ ታሪፍ እና ታሪፍ ያልሆኑ ገደቦች ሊነሱ ይገባል- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- አፍሪካ በአውሮፓ ገበያ ውስጥ ያላት ድርሻ እና ተደራሽነት እንዲጨምር ታሪፍና ታሪፍ ያልሆኑ ገደቦች መነሳት እንደሚገባቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

ሰባተኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በአንጎላ ሉዋንዳ ተጀምሯል።

ጉባኤውን የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆአኦ ሎሬንቾና የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት አንቶኒዮ ኮስታ በጋራ መርተውታል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ የህብረቱ ሀገራት መሪዎች፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ወጣቶች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የንግድ ልዑካን በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በቅርቡ የዓለም እድገት ኃይል ምንጭ እንደምትሆን ገልጸዋል።

የተትረፈረፈ የገበያ እድል፣ የሰው ኃይል እና የተፈጥሮ ሀብቶች የዓለም እድገት ዋንኛ ተዋናይ የሚያደርጓት አቅሞች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሊቀ መንበሩ በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ሚዛናዊ የሆነ የንግድ አጋርነት ሊኖር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በአፍሪካ ያለው የአውሮፓ ኢንቨስትመንት መጨመር እንዳለበትም አንስተዋል።

አፍሪካ ሀገራት ወደ አውሮፓ ህብረት ገበያ በሚፈለገው መጠን እንዳይገቡ ያደረጋቸው የታሪፍ እና ከታሪፍ ጋር ያልተያያዙ ገደቦች እንዲነሱም ጠይቀዋል።

እኩልነት እና የጋራ ፍላጎቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ጠንካራ የባለብዙወገን ትብብር መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰላም፣ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት፣ ፍልሰት እና የሰዎች እንቅስቃሴና የሰው ኃይል ልማት መሪዎቹ ውይይት ከሚያደርጉባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የተቋማቱ መሪዎች ለባለብዙ ወገን ትብብር፣ አጋርነት እና እየታዩ ላሉ ፈተናዎች የተቀናጀ ምላሽ የመስጠት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የሚወያዩባቸው ጉዳዮች በአጀንዳ 2063፣ በዘላቂ የልማት ግቦች እና የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የ2030 የጋራ ራዕይ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ከዋናው የመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ የወጣቶች እና የሲቪክ እንዲሁም የንግድ ፎረሞች መካሄዳቸው ይታወቃል።

ሰባተኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እስገ ነገ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም