ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት እያስመዘገበች ያለው ውጤት እንዲያድግ የበለጠ መስራት ይገባል- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም እና አህጉራዊ  የውድድር መድረኮች ላይ በብስክሌት ስፖርት እያስመዘገበች ያለው ውጤት እንዲጠናከር አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፀጋዬ ማሞ ገለጹ። 

በኬንያ ክዋሌ ከተማ በተካሄደው 19ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። 

ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፀጋዬ ማሞ እና የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል። 

ሚኒስትር ዴኤታ ፀጋዬ ማሞ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ምቹ ዕድል እንደ ሀገር አሸናፊ ቡድን ለመገንባት ማስቻሉን ተናግረዋል። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ልክ እንደ አትሌትክሱ ሁሉ የአረንጎዴ ጎርፍ ታሪክን እየደገመ ነው ሲሉ ገልጸው ውጤት ለማሳደግ የበለጠ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። 

መንግስት ለብስክሌት ስፖርት የሚያደርግውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ብስክሌት ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድሙ ኃይሌ ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት የምትኮራባቸው ስፖርተኞች ተፈጥረዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

በኬንያ የተካሄደው ሻምፒዮና የአፍሪካዊያን ዓይን ወደ ኢትዮጵያ ያዞረና ባንዲራችን እንዲውለበለብ ያደረገ ነው ብለዋል። 

ውድድሩ ለብስክሌተኞቹ በቀጣይ በዓለም የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ እንዲሳተፉ እድል የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል። 

በ19ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ከ29 ሀገራት የተሳተፉ ብስክሌቶች የተወዳደሩ ሲሆን ኢትዮጵያም በሁለቱም ጾታዎች 10 ብስክሌተኞች አሳትፋለች።

በዚህም ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎቹ በአዋቂ፣ ታዳጊ ወጣቶች እና ከ23 አመት በታች ተሳትፈዋል። 

በዚህም በብስክሌተኛ ፅጌ ካህሳይ  በግል ሰዓት ሙከራ ውድድርና በጎዳና ላይ ውድድር  ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ አግኝታለች። 

በጎዳና ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ ቅሳነት ግርማይ 3ኛ ደረጃ ይዛ ነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ስታጠናቅቅ ራሄል ታመነ 4ኛ በመውጣት በአጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም