የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ።
የሥርዓተ- ጾታ ኦዲት መንግስት የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁትን ሥርዓተ- ጾታ ኦዲት ሰነድ የማስተዋወቅ መርሃ-ግብር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመንግስት ተቋማት በሚያከናውኗቸው ተግባራት የሥርዓተ- ጾታ እኩልነት ጉዳይን አካትተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ መመልከት እንደሚገባ ተገንዝቦ የሥርዓተ -ጾታ ኦዲት ሰነድ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ይህም ሁሉን አቀፍ ኦዲት ለማካሄድ ያለውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተትን በመቅረፍ ተቋማዊ አቅምን ከማጠናከር ባለፈ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አካታችነትን እንዲሁም የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አሳልፈው አመዲን የሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ማህበራዊ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት በመፈራረም የስርዓተ-ጾታ እኩልነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በፌዴራል ዋና ኦዲተር እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ኤጀንሲ ትብብር የተዘጋጀው የሥርዓተ- ጾታ ኦዲት ሰነድ የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ኤጀንሲ ምክትል ተጠሪ ሻራክ ዱሳቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሥርዓተ- ጾታ ኦዲት ትግበራ የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል።
የሥርዓተ- ጾታ ኦዲት ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም ዙርያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየትና ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በፌዴራል ዋና ኦዲተርና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትብብር የተዘጋጀው ሰነድ በጾታ እኩልነት፣ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ትብብርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡