ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታዳሚዎች መልካም መስተንግዶ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -በሆሳዕና ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታዳሚዎች መልካም መስተንግዶ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -በሆሳዕና ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት
ሆሳዕና፤ ህዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን በሆሳዕና ከተማዋ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በከተማዋ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የተሟላ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሃሳብ በሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡
በሆሳዕና ከተማ በዓሉ መከበሩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዳሉት በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ለመቀበል ተዘጋጅተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የገብረፃዲቅ ሆቴልና ስፓ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ሙሌ እንደገለፁት ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የእንግዶችን ምቾት የሚያስጠብቁ የሆቴል አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የአካባቢውን ወግና ባህል ለማስተዋወቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
"ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ መስተንግዶ ለመስጠትና ንፁህ የመኝታና የማረፊያ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል" ሲሉም ነው የገለጹት።
ሌላኛው የትንሳኤ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ብርሃኑ በበኩላቸው ሆቴሉ እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ በመቀበል ተደስተው እንዲመለሱ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሀዲያን ህዝብ ለክብር እንግዳ የሚያዘጋጀውን "አተካና" የተሰኘ ባህላዊ ምግብ ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት እንግዶችን ለመቀበል የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከከተማው የታክሲ አሽከርካሪዎች መካከል ተመስገን ኢቲቦ ፤ ለበዓሉ ታዳሚዎች ከሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ የአካባቢውን የመዝናኛና የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
አቶ አማረ ገብረሃና የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የሚመጡ እንግዶችን በበጎ ፍቃደኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ፤ በሃገር ደረጃ የሚከበረውን 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ባማረና በደመቀ መልኩ እንዲከበር አስትዳደሩ የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የተጀመሩ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ከማጠናቀቅ ጀምሮ ነባሮቹም ለእንግዶች ተገቢውን አገልገሎት እንዲሰጡ የማዘጋጀት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች የከተማዋን የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ የሚደረግበት ሁኔታ መመቻቸቱን ጠቅሰው፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንግዶችን ተቀበልው እንዲያስተናግዱ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡