በጎንደር የቱሪዝም ልማቱና የከተማው ማስዋብ ስራዎች የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር የቱሪዝም ልማቱና የከተማው ማስዋብ ስራዎች የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል
ጎንደር፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር እየተከናወነ ያለው የቱሪዝም ልማትና የከተማው ማስዋብ ስራዎች የውጭና የሀገር ውስጥ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።
የዘንድሮ የጎንደር የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነትን በሚያስተሳስስር መንገድ ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ዝግጅቱን በመገምገም ክትትልና ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ስራ የጎንደር ከተማን ዳግም ትንሳኤ ያበሰረ ታላቅ ታሪካዊ ክዋኔ ነው፡፡
ጥምቀትን ለማክበር የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የታደሰውን ቤተ መንግስት እንዲጎበኙ በማድረግ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራም ለበዓሉ ልዩ ድባብን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማው ሕዝብም እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ አይረሴ ቆይታ እንዲኖራቸው እንዲያደርግ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በጎንደር እየተከናወነ ያለው የቱሪዝም ልማትና የከተማው ማስዋብ ስራዎች የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ለመጨመር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በስኬት ለማክበር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በመገምገም ቀሪ ተግባራትን በማመላከት ፈጥነው እንዲተገበሩ ለማስቻል በሥፍራው ተገኝተው ድጋፍ ማድረጋቸውን የቢሮው ሃላፊ አቶ መልካሙ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በርካታ የሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችና ባሕላዊ እሴቶች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፤ በወርሃ ጥር የሚከበረው የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ እነዚህን ቅርሶች ለማስተዋወቅ አጋዥ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
በክልሉ ነባርና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት፣ በመጠበቅና በመንከባከብ መንግስት እያከናወነው ያለው ተግባር ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ማሪያሟ ካሳሁን በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓልን በስኬት ለማክበር በዐቢይ ኮሚቴ የሚመራ ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ አብሮነት፣ ወንድማማችነትና አንድነትን የሚያስተሳስርና የሚያጠናክር የባሕል ፌስቲቫል ከበዓሉ አንድ ሳምንት ቀድሞ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል።
በፌስቲቫሉ ላይም ባሕላዊ እሴትና ትውፊቶችን የሚያንጸባርቁ የጎዳና ላይ ትዕይንቶች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ ይህም የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም የከተማውን ሕዝብ ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።