ቀጥታ፡

በአፋር ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሠመራ፣ ህዳር 15/2018(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት  እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉ  ተገለጸ። 

በክልሉ ወሰማ ወረዳ የተገነባው አዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑሩ፤  ከሃገራዊ ለውጡ ወዲህ የክልሉ መንግሥት፣ ሕብረተሰቡን፣ ባለሀብቶችንና ሌሎችንም አጋር አካላት በማስተባበር የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

ይህም ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በወሰማ ወረዳ  የተገነባው ትምህርት ቤት ላለፉት ዓመታት ሕብረሰተቡ ሲያናሳው ለቆየው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይነትም ለትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች በማሟላት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ የክልሉ መንግስት ተከታትሎ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሳ አደም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ትምህርትን በፍትሃዊነት ማዳረስ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ነው።

ለምረቃ የበቃው ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል አብአላና በራህሌ ድረስ ረጅም ርቀት ይሄዱ የነበረውን ያስቀረ መሆኑንም ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቱ የተገነባው የትምህርት ቢሮና ኢዱካንሰ ፋውንዴሽን ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በ14 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑን አስታውቀዋል።

የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ለሜሳ፤ መንገስት የትምህረት ተደራሽነትን ለማስፋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የወረዳ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም