ቀጥታ፡

የትራፊክ ደህንነትን በማረጋገጥ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርስን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ህዳር 15/2018(ኢዜአ):- የትራፊክ ደህንነት በማረጋገጥ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርስን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ። 

አገልግሎቱ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሀገራዊ የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡ 

የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት የህግ ትግበራ ባለሙያ አቶ ማህተመ ታደሰ  በወቅቱ እንዳሉት የትራፊክ ደህንነትን በማረጋገጥ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርስን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ ነው።

በዚህም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሰባት ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

ይህም መርሃ ግብር የአሽከርካሪዎችን ግንዛቤ በማሳደግ በአሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ጉድለት የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ማለሙንም ተናግረዋል።

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የባለድርሻ አካላት ትብብርን በማሳደግ ከግንዛቤ ፈጠራ ባለፈ የተሽከርካሪ ደህንነት ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ላቾሬ በበኩላቸው ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የትራፊክ አደጋ በመጨመሩ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡ 

የትራፊክ አደጋ ቀውስን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ወጤት እየታየ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር መከናወኑን አመልክተዋል። 

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ቁጥጥርና ግንዛቤ ላይ ትኩረት መደረጉን የገለጹት ደግሞ በክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ አስተዳደር ቢሮ የመንገድ ደህንነት ባለሙያ ወይዘሮ ሰርካለም ሙሉጌታ ናቸው።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በቅንጅት ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው ለተግባራዊነቱ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች የመንገድ ደህንነት ህጉን በማክበር ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁም አሳስበዋል። 

በወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ሳጅን ዝናቡ ገዛኸኝ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከፌደራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰራ በርካቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል አንስተው ቁጥጥሩ በከተማው ደረጃ ላሉ የትራፊክ ፖሊሶች በቂ ግንዛቤ ለመስጠት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አሽከርካሪ አሳምነው ወጋሶ ሙያው የሚጠይቀውንና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ምክር በመተግበር አደጋ እንዳይደርስ በጥንቃቄ እንደሚያሽከረክሩ ገልጸዋል፡፡ 

አሽከርካሪ የቤተሰብና የሀገር ሃላፊነት ያለባቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን ደህንነት ጠብቆ ወደ ሚሄዱበት የማድረስ ኃላፊነት ተጥሎበታል ያሉት ሌላው አሽከርካሪ ፍጹም ግንዳቦ ናቸው።

ይህን በመረዳት  በጥንቃቄ በማሽከርከር አደጋ እንዳይደርስ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም