የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ስራዎች ለዓለም ለማሳወቅ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል- ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ስራዎች ለዓለም ለማሳወቅ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል- ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፏ እያከናወነቻቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቡድን 20 አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሄዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ይህን አስመልክቶ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በቡድን 20 ላይ የተጋበዘቸው መታየት ያለባቸው መስፈርቶችን ስላሟላች ነው፤ ከተጋበዙ ሀገራትም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል ናት ብለዋል።
በዚህም መሠረት በኢኮኖሚ መጠን፣ ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ባላት ሚና እንዲሁም አሁን እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን መሠረት በማድረግ በስብሰባው ላይ መጋበዟን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ መድረኩ የአፍሪካ ሀገራት ድምጽ እንዲሰማበት ማድረግ የሚያስችል ሐሳብ ማንሳታቸውንም አመላክተዋል።
የዓለም አሥተዳደር፣ የኢኮኖሚ ብሎም ፋይናንስ አሥተዳደር እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው ያነሱት።
መድረኩ ኢትዮጵያ እየሠራች ያለውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ለመግለጽ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል ሚኒስትሯ።
የኢትዮጵያ ድምጽ ትልቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ስብሰባ በተጋባዥነት መሳተፏ የኢትዮጵያን መታየት በደንብ አድርጎ መጨመሩን ተናግረዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየች ያለው ዕድገት፣ ካላት የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛት በአጠቃላይ ካለችበት ለውጥ አንጻር ዝም ልትባል አትችልም ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በመድረኩ ብዝኀ ወገን የሚለው ሐሳብ አዋጭ መሆኑን አንስተዋል፤ አፍሪካን በየትኛውም ዘርፍ ያላካተተ አካሄድ የትም እንደማይደርስም ተስተጋብቷል ብለዋል።
ከስብሰባው ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከበርካታ ሀገራት መሪዎች ጋር መምከራቸውን ገልጸው፤ ውይይቶቹ የሚያሳዩት የኢትዮጵያ ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።
መሪዎቹም የኢትዮጵያን ልማት እንዲደግፉ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዙሪያ ውይይቶች መደረጋቸውን አመላክተዋል።
በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው ስብሰባ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ፤ የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም አንስተዋል።