ኬንያ ደቡብ ሱዳንን አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
ኬንያ ደቡብ ሱዳንን አሸነፈች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካ ዞን ማጣሪያ ኬንያ ደቡብ ሱዳንን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው የምድብ አንድ ጨዋታ ዴሪክ ዋንዮንዪ በ12ኛው እና ትሬቨር ናሳሲሮ በ89ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ድሉን ተከትሎ ኬንያ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ደቡብ ሱዳን በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በዚሁ ምድብ ዛሬ በተካሄደ ጨዋታ ሶማሊያ ሩዋንዳን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
የማጣሪያው አዘጋጅ ሀገር ኢትዮጵያ ምድቡን በሰባት ነጥብ እየመራች ትገኛለች።
በተያያዘም በምድብ ሁለት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ታንዛንያ ብሩንዲን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።
ሳዳም ሁሴኒ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሲሰራ እድሪሳ ካይለንዴሞ እና ኢስማኤል ላይኩንጊሎ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ታንዛንያ በ12 ነጥብ የምድብ መሪነቷን አጠናክራለች። በብሄራዊ ቡድን ለግማሽ ፍጻሜው ያለፈ የመጀመሪያ ቡድን መሆኑ ይታወቃል።
በዚሁ ምድብ ጅቡቲ ከሱዳን ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።