ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቡድን 20 መሪዎች ጉባኤ ተሳትፎ በዓለም የባለብዙወገን መድረኮች እያደገ የሚገኘውን ሚናዋን በግልጽ ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ያደረገችው ተሳትፎ በዓለም የባለብዙወገን መድረኮች እያደገ የመጣውን የዲፕሎማሲ ሚና በግልጽ የታየበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

የቡድን 20 አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ተካሄዷል።

ጉባኤው በአፍሪካ የተካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተሳተፉበት የቡድን 20 ጉባኤ እና የጎንዮሽ ውይይቶችን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ጋባዥነት በጉባኤው ላይ መሳተፏን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከበርካታ ሀገራት መሪዎች እና የባለብዙ ወገን ተቋማት ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው አዘጋጅ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ ጋር መወያየታቸውንና ውይይቱ በጉባኤው የአፍሪካን የጋራ ድምጽ እና ፍላጎት ማሰማትና ማንጸባረቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአቡዳቢ አልጋ ወራሽ ሼክ ካሌድ ቢን መሐሙድ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታመር፣ ከኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ሾፍ እና ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር መምከራቸውን አመልክተዋል።

ከእስያ ሀገራትም መካከል ከቪዬተናም፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢንዶኔዥያ መሪዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በባለብዙ ወገን መድረክም ከተባበሩት መንግስት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና ከዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ጋር መምከራቸውንም እንዲሁ።

በአፍሪካ ደረጃም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲድ ኡልድ ታህ ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን መድረክ እያደገ ያለውን ቁመና በማንሳት የበለጠ ትብብሮችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ነው ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ ያብራሩት።

በሌላ በኩል በውይይቶቹ ኢትዮጵያ እያደረገች የምትገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ያስገኟቸው አመርቂ ውጤቶች እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እንዲሁም የኢኮኖሚ ማረጋጋት ተግባራት መነሳታቸውን ገልጸዋል።

ሀገራትና ተቋማቱ ማሻሻያዎቹን እንዲደግፉም ጥሪ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ እያደገ የመጣው ሚናዋ ሌላኛው የውይይቶቹ ትኩረት ነበር።

ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ ኢትዮጵያ በቅርቡ 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ(ኮፕ 32)ን እንድታስተናግድ መመረጧን አውስተው፤ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድና ሁሉን አካታች እንዲሆን አጋሮች ድጋፍ በሚያደርጉበትና ኢትዮጵያ ልምድ በመቅሰም በምትችልበት ሁኔታ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል።

ጉባኤው በሺዎች የሚቆጠሩ የሚሳተፉበት በመሆኑ ለቱሪዝም ልማት፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ እና ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን በተካሄደው የኮምፓክት ፎር አፍሪካ ስብሰባ ላይ በመሳተፍ ባደረጉት ንግግር የበለጸጉ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ውጤታማ እና ፍሬያማ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የጉባኤው ተሳትፎ በዓለም የባለብዙወገን መድረኮች ላይ ያላት ቁመና የበለጠ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም