የቢሾፍቱ የኮሪደር ልማት የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ የኮሪደር ልማት የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋ የቱሪዝም ፣ የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማስቻሉን ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ቢሾፍቱ በሶስት ክፍለ ከተሞች እና በአስራ አንድ ወረዳዎች የተደራጀች ከተማ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ ከዚህ በፊት 32 ሺህ ሔክታር የቆዳ ስፋት እንደነበራት አስታውሰው፤ አሁን ላይ አቅራቢያዋ የሚገኙ ትንንሽ ከተሞችንና የገጠር ቀበሌዎችን በማካተት ወደ 63 ሺህ ሔክታር የቆዳ ስፋት ማደጓን አመላክተዋል፡፡
ለከተማዋ እድገት የያዘቻቸው ተፈጥሯዊ ሃብቶችና የመልማት እምቅ አቅሞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቢሾፍቱ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉና የከተማዋ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማስቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በኮሪደሩ ልማት አዳዲስ የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች፣ የስብሰባ ማዕከላትና አንፊ ቲአትሮች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ የከተማዋ የቱሪዝም፣ የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩን ገልጸው፤ ይህም የከተማዋ ገቢ እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል
በዚህም ከአምስት ዓመታት በፊት የከተማዋ ገቢ ከ1 ቢሊዮን ብር በታች እንደነበር አውስተው፤ አሁን ላይ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ወደ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡
ለቢሾፍቱ ከተማ ልማት የመንግስት እና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አመላክተው፤ በቀጣይም የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑ እና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡