የኢትዮጵያ ታዳጊዎች እምቅ የእግር ኳስ ተሰጥኦ በአጭር ጊዜ አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ተስፋ የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታዳጊዎች እምቅ የእግር ኳስ ተሰጥኦ በአጭር ጊዜ አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ተስፋ የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት የጀመረችው ጥረትና የታዳጊዎቿ እምቅ የተሰጥኦ አቅም በአጭር ጊዜ ጠንካራ ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደምትችል ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ በይፋ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ለዚህም መንግሥት በስፖርት መሰረተ ልማትና ብቁ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቷል፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም "ጉዞ ለ2029" በሚል መርህ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ እምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣት ተጫዋቾች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2029 በአፍሪካ ዋንጫ ተፎካካሪና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር ያስቀመጠው ግብ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ታዳጊዎቹ ለእግር ኳስ ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገባውን የእግር ኳስ ናፍቆት የሚመልስና የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚያሳካ እምቅ አቅም እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አባላትንም "ያልተቆረጠ አልማዝ" ሲሉ ያላቸውን እምቅ ችሎታ አወድሰዋል፡፡
መንግሥት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት የሚወስዳቸው ቁልፍ እርምጃዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የገለጹት አሠልጣኙ፤ ከ15፣ 17፣ እና 20 ዓመት በታች ባሉ የዕድሜ ምድቦች ታዳጊዎችን የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአሠልጣኞች እና በወጣቶች አቅም ግንባታ የጀመረውን ጥረት በማድነቅ፤ ወጣቶች በሌሎች ሀገራት ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግና የሊግ ጨዋታዎችን አወቃቀር ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ እግር ኳስ ይገባዋል ያሉት አሠልጣኙ፤ ለዚህ ደግሞ የወጣቶችን እምቅ አቅም በጋራ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡