ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲንጋፖር ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲንጋፖር ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲንጋፖር ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግን ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የሲንጋፖር ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግን በክብር መቀበላቸውን ገልጸዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ለጋራ ነጋችን ወሳኝ በሆኑ መስኮች በጋራ ለመሥራት በምናደርገው ጥረት ውስጥ አንድ ጠቃሚ ርምጃ ነው ብለዋል።
በተለይም በክሂሎት ልማት እና የካርበን ብድር ትብብር ላይ ያደረግናቸው የመግባቢያ ስምምነቶች ጽኑ እና ለነገው ገበያ ዝግጁ የሆኑ ሠራተኞችን ለማፍራት ብሎም በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ ዘላቂ፣ ዝቅተኛ ካርበን የሚያወጣ እድገት ለማረጋገጥ ያለንን የጋራ አቋም የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከሲንጋፖር ጋር ይኽን የወዳጅነት እና የትብብር ጉዞ በጋራ በመቀጠላችንም ክብር ይሰማናል ሲሉ ተናግረዋል።
በላቀ ተግባራዊ ትብብር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስን በማልማት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣ በገንዘብ ልውውጥ ቴክኖሎጂ፣ ሳይበር ደኅንነት እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለንን ትብብር ለመጠቀም እጅግ ሰፊ አቅም እንዳለም አንስተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።