ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በመኸር ሰብል አሰባሰብ ላይ የሚኖረውን ብክነት ለመቀነስ ኮምባይነር እና አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም ምርቱ እየተሰበሰበ ነው

አዳማ፤ ህዳር 15/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በመኸር ሰብል አሰባሰብ ላይ የሚኖረውን ብክነት ለመቀነስ ኮምባይነር እና አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የመኸር ሰብል አሰባሰብ በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ በይፋ ተጀምሯል።

የቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሶ ፈይሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ከ10 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሄክታር በመኸር እርሻ መሸፈኑን ገልጸዋል።

የ2017/18 የምርት ዘመን አብዛኛው በኩታ ገጠም የተዘራ በመሆኑ በተለይ ተመሳሳይ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን አርሶ አደሩ በስፋት መጠቀሙን ተናግረዋል።

በዚህም መከናይዜሽን፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በባለሙያዎች ተደግፎ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

በዚህም ሰብሉ የተሻለ ቁመና ላይ መሆኑን አንስተው በሄክታር በአማካይ ከሄክታር ከ30 ኩንታል በላይ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በምርት ዘመኑ 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ እስካሁን በተደረገ የመሰብሰብ ጥረት ከ60 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

የመኸር ሰብል የማንሳት ስራው በሰው ሃይልና በመካናይዜሽን እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ምርቱን ከብክነት ከመታደግ ባለፈ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ ኢብራሂም ከድር በበኩላቸው በዞኑ 1 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመኸር እርሻ መልማቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም 5 መቶ ሺህ ሄክታሩርበስንዴ በኩታ ገጠም መልማቱን ተናግረዋል።

በዚህም በምርት ዘመኑ ከ32 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው በተለይ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም