ቀጥታ፡

የመልካጀብዱን የአስፋልት መንገድ በቀጣይ ሁለት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ፤፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- የወጪና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው የመልካጀብዱ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት እየተፋጠነ  መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር  የድሬዳዋ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት አስታወቀ።

 የመንገዱ ግንባታ በቀጣይ ሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅም ተመላክቷል።


 

በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት በሁለት አቅጣጫ እየተፋጠነ የሚገኘው የመልካ ጀብዱ የመንገድ ፕሮጀክት፤ መልካጀብዱን ከድሬዳዋ እንዲሁም መልካን ከነፃ ንግድ ቀጠና ጋር በማስተሳሰር ወደ ጅቡቲ ከሚጓዘው የአስፋልት መንገድ ጋር የሚያገናኝ ፕሮጀክት ነው።

በወሰን ማስከበር  ምክንያት  ላለፉት ሰባት አመታት  የተጓተተው ፕሮጀክት  የድሬዳዋ አስተዳደር  ካሳውን  በመክፈል  የፌደራል መንግስት መንገዱን ዳግም  ወደ ስራ ማስገባቱን በዲስትሪክቱ የመልካጀብዱ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር ደረሰ እሸቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ሰአትም የፕሮጀክቱ አካል የሆነ የ2 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የአንዱ አቅጣጫ ተጠናቅቆ ለተሽከርካሪዎች ክፍት መደረጉም ተጠቅሷል።

ፕሮጀክቱም 70 በመቶ መገባደዱ እና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ኢንጂነር ደረሰ ገለፃ ይህ ፕሮጀክት የወጪና ገቢ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚዘወሩበት የድሬዳዋ ትልቁ የለውጥ መንገድ ነው።


 

ፕሮጀክቱ ድሬዳዋን ከጅቡቲ ጋር ከሚያስተሳስረው መንገድ ጋር  የሚያገናኝ በመሆኑ ለድሬዳዋ  እና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ፤ የመንገዱ መጠናቀቅ የወጪና ገቢ ንግድን በማሳለጥ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያፋጥን ገልጸዋል።


 

ወደ ጅቡቲ ሲጓዝ የነበረው የከባድ መኪና አሽከርካሪ ወጣት ኤፍሬም ወልደዮሐንስ ፤ መንገዱ በዚህ መልክ አምሮ መሰራቱ የመኪኖችን  ደህንነት በማረጋገጥ ለተስተካከለ ትራፊክ ፍሰት ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም