ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018(ኢዜአ)፦ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) ይበልጥ ለማጎልበት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ አባል እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ገለጹ።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበት 55ኛ ዓመት ይከበራል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የሀገራቱን 55ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ የደስታ መግለጫ መልዕክት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) አስተላልፈዋል።
ዋንግ ዪ በመልዕክታቸው ቻይና እና ኢትዮጵያ ጥልቅ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው ግንኙነታቸው በዓመታት መካከል ፀንቶ መቀጠሉን አመልክተዋል።
ባለፉት 55 ዓመታት ሁለቱ ሀገራት የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመልካም እምነት ላይ እና በአስፈላጊ ጊዜ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አመልክተዋል።
ወዳጅነቱ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት አጋርነትና ትብብር ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራቱ መሪዎች ስትራቴጂካዊ መሪነት የሁለትዮሽ ትብብሩ የበለጠ እየጠነከረ መምጣቱንም ነው ያመለከቱት።
ከምንጊዜውም በላይ የዳበረው የፖለቲካ የጋራ መተማመንና ፍሬያማ ተግባራዊ ትብብር መገለጫው የሆነው የሁለትዮሽ ግንኙነት ለሀገራቱ ህዝቦች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስገኘቱን አብራርተዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የ55ኛ ዓመቱን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዓል እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም(ፎካክ) ጉባኤ ውጤቶችና የሀገራቱ መሪዎች የጋራ መግባባት ላይ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመተግበር እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) የበለጠ ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
በሁኔታዎች የማይለዋወጥ የጋራ ራዕይን ማዕከል ያደረገ የቻይና-አፍሪካ ማህበረሰብ አዲስ የትብብር ምዕራፍ በመክፈቱ ላይ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ